20/06/2026
በሴቶችና ህጻናት ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የህክምና ማስረጃ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ሰኔ 13/2018 ዓ/ም
********//********
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ንግስት እሌኒ መሃመድ መታሰቢያ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነት፤ ከሀድያ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ከተወጣጡ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ ዓቃቤ ህጎች፣ መርማሪ ፖሊሶች እና በሆስፒታሉ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ (One-Stop Center) ከሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በሆሳዕና ከተማ በተደረገ ውይይት በሴቶችና ህጻናት ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የህክምና ማስረጃ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ን/እ/መ/መ/ኮ/ስ/ሆስፒታል የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተክሌ እጃጆ በንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት፦ በአሁኑ ሰአት የሆስፒታሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በአንድ ማዕከል (One-Stop Center) ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ፣ ለተጎጂዎች የስነ-ልቦና ድጋፍ ይሆን ዘንድ የ72 ሰዓት ማቆያ እንዲሁም የሕፃናት የስነ-ልቦና ሕክምና ማዕከል በመደራጀት ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ጥራት ያለው የሕክምና ማስረጃ ለፍትህ አካላት ለማቅረብ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም አቶ ተክሌ እንደተናገሩት ይህን መሰል ውይይቶች በሕግ ባለሙያዎችና በሐኪሞች መካከል ግልጽ አሰራርን ስለሚፈጥር ለፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመጠቆም ይህንን ውይይት ወደፊትም ከፍትህ አካላት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሀዲያ ዞን የሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ቴሬዛ አለሙ እንደተናገሩት፦ ሆስፒታሉ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነትን ይህ የተዘጋጀው የሐኪሞችና የሕግ ባለሙያዎች ውይይት ያሳያል በማለት ይህም በአንድ ማዕከል በሚሰሩ ፎረንሲክ ሐኪሞች፣ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቶች እና በሕግ ባለሙያዎች መካከል ጠንካራ የተግባቦት አሰራር ስለሚፈጥር፣ ጥቃቱን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከሆስፒታሉ ከአንድ ማዕከል አገልግሎት (one stop center) የተወጣጡ የህክምና ባለሞያዎች በሕክምና ማስረጃ ዙሪያ ሳይንሳዊ በሆኑ የቃላት መግለጫዎች ላይ እንዲሁም ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ልዩ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
ዘገባው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ን/እ/መ/መ/ኮ/እ/ ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ነው!!!
Let Your light shine in the Society!!
ስለ ጤናዎ ለማማከር ዘውትር ከ ሰኞ-እሁድ በነጻ የስልክ መስመር 6712 ላይ ይደውሉ!!