17/08/2026
ውሻ የማይወድ ሰው አላምንም!?
የፈረንጅ ልጆች የቤት እና ዱር እንሰሳትን ሲያዩ ፣ የምናስተውለው በስስት አቅፈው አብረዋቸው ለመጫወት ሲሞክሩ ነው። በአንፃሩ ፣ የእኛ 'ፈላዎች' እንስሳት ሲያዩ ዓይናቸው ድንጋይ ፍለጋ ያማትራል። ልጆቻችን ውሻ ፣ ጦጣና አእዋፋትን ሲያዩ ደስታቸውን የሚገልፁት እንስሳቱን አባረው በመውገር ነው። እኛም በልጅነታችን አድርገነዋል። በወላጆቻችን እና በእንስሳት መካከል የነበረው ግንኙነትም የአዳኝ እና ታዳኝ ነበር።
እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ ፣ የልጆች ቡረቃ ምንጭ አቅም አልባ ፍጡራንን መምታት ሲሆን ፣ ልምምዱን አንድ ተራ ልምምድ ተረድቶ ማለፍ ይቸግራል። የደስታችን ምንጭ የሌሎች ስቃይ ከሆነ ስነ ልቦናዊ ዝንፈት አለ ማለት ነው። ለጦጣ ድንጋይ የሚያነሳ ማቲ ፣ በቤቱ በረባ ባልረባ ጥፋቱ ለአርጩሜ የተዳረገ ነው። ከውሻ ጋር ከመጫወት ይልቅ ፣ ውሻን ማቁሰል የሚያስፈነድቀው ልጅ 'ቫዮለንስ'ን የቀመሰ ወይም የተመለከተ ነው። ልጆች ሰብዕናቸው የሚቀረፅበት አንዱ መንገድ 'ኤሚቴሽን' ይባላል። ልጆች ወላጆቻቸው/አሳዳጊዎች የሚያደርጉትን ገልብጠው ያደርጋሉ። በዱለኛ ወላጅ እጅ የሚያድግ ልጅ ፣ ጨዋታው እንኳን ከኃይል ጋር የተቀላቀለ ነው። እንዲህ ዓይነት ልጅ ጦጣ ሲያይ ፣ አባሮ መምታት እንጂ አቅፎ መሳም አይታየውም።
ይሄ ልምምድ ስለ ልጆቹ የነገ ማንነትም ይናገራል። ሳይኮሎጂስቶች የአዋቂነት ማንነታችን የልጅነታችን ነፀብራቅ ወይም ተቀርኖ ነው (who we are today is the reflection and/or reaction of our childhood experiences)" ይላሉ። ዛሬ ጦጣን በመምታት የሚደሰት ልጅ ፣ ነገ ከበታቹ የሚሰሩ ሰራተኞችን በማጎሳቆል የሚታወቅ ሊሆን ይችላል። 'ዲፌንስለስ' ፍጡራንን ማባረር የሚያስቦርቀው ታዳጊ ፣
እንስሳትን የማያከብር ፣ ፈርቶ ካልሆነ በቀር ፈቅዶ ለሰው ልጅም አያዝንም። እንሰሳ ወዳጅ ልጆች ሰው አፍቃሪም ይሆናሉ። አንድ ጓደኛዬ 'ውሻ የማይወድ ሰው አላምንም' ትላለች። አስተሳሰቧ ከውሻ ፍቅሯ የመነጨ ቢሆንም ፣ መጠነኛ ስነ ልቦናዊ ሀቅም አለው። ሁላችንም አንድ ልብ ነው የተሰጠን። ለአንዱ አዝነንበት ለሌላው ልንጨክንበት አንችልም። እንስሳት የሚጠላ ልቦና ፣ ለሰብዓዊ ፍጡርም ግድ የለሽ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው። እውነተኛ ማንነታችን አቅም አልባ እና ከእኛ ከሚለዩ ፍጡራን ጋር በሚኖረን ግንኙነት በጣሙኑ ይገለፃል። አስተናጋጆችን የሚያመናቅር ወንድ ለሴት ፍቅረኛው ጥልቅ ክብር አይኖረውም። የቤት ሰራተኛ የሚበድል ፣ ለሰራተኞቹ አይራራም። እንስሳትን የሚያጎሳቁል ለሰው ልጆች (ያለ ልዩነት) አዛኝ አይሆንም።