05/09/2026
በዘርፉ ህመምን ከመቆጣጠር ባሻገር ስቃይን ማስታገስና የኑሮ ጥራትን ማሻሻል እንደሚገባ ተገለፀ
በ“Basic Pain and Palliative Care” አገልግሎት ላይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30/ 2018 ዓ.ም – በህክምና ሂደት ወቅት ታካሚዎች የሚያጋጥማቸውን ህመምና ስቃይ በተገቢው ለመለየት፣ ለመገምገም፣ ለመቆጣጠርና ለማስታገስ የሚያስችል “Basic Pain and Palliative Care” አገልግሎት ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከሆስፒታሉ ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ተያያዥ የዘርፍ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ተሰጠ።
ስልጠናው በአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋሚሊ ሜዲስን ስፔሻሊስት ሀኪም በሆኑት ዶ/ር ሚኪያስ ታደለና የህክምና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ነው።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የስነ-አእምሮ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ዶ/ር ሉሉ በቃና ሲሆኑ በንግግራቸው “ የምንሰጠው አገልግሎት ማከምና ማዳን ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት ህመምንና ስቃይን መቀነስ መቻል የጤና አገልግሎት ጥራት ወሳኝ አካል ነው” ብለዋል።
ዶ/ር ሉሉ እንደገለፁት የስልጠናው ዋና ዓላማ የታካሚዎችን ህመምና ስቃይ በአግባቡ በመረዳት ተገቢውን እንክብካቤና የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ማጎልበት ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሚኪያስ ታደለ በበኩላቸው ስልጠናው የጤና ባለሙያዎች የታካሚዎችን የህመም ደረጃ በተገቢው እንዲመዝኑ፣ ተገቢውን የህመም መቆጣጠሪያ አማራጭ እንዲመርጡና በህክምና ሂደቱ ውስጥ ሰው-ተኮር እንክብካቤን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም የአእምሮ ህመም ያለባቸው ታካሚዎች ህመምና ስቃያቸውን የሚገልጹበት መንገድ ከሌሎች ታካሚዎች ሊለይ ስለሚችል ህመማቸውን በትክክል መለየትና መገምገም ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑንም በማከል ገልጸዋል።
ፓሊያቲቭ ኬር (Palliative Care) ማለት ህመምን ማከም ብቻ ሳይሆን በከባድና ረጅም ጊዜ ህመም የሚሰቃዩ ታካሚዎችን በሙሉ የሰውነት እና የሰውነት ውጭ ፍላጎቶች በመመልከት የኑሮ ጥራታቸውን ለማሻሻል የሚሰጥ የተቀናጀ እንክብካቤ ነው።
አገልግሎቱ ከህመምና ከሌሎች አስጨናቂ ምልክቶች እፎይታ ከመስጠት ባሻገር የታካሚውን አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በተቀናጀ መልኩ በማገናዘብ ምላሽ የሚሰጥበት ህክምና ነው። በዚህም ታካሚውና ቤተሰቡ በህመም ሂደት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ጫና ለመቀነስና የኑሮ ጥራታቸውን ለማሻሻል ያግዛል ማለት ነው።
በስልጠናው ላይ የህመም ምንነትና አይነቶች፣ የህመም መጠንን መመዘንና መከታተል፣ የህመም ማስታገሻ ዘዴዎች፣ የታካሚዎችን ስቃይ ለመቀነስ የሚያግዙ የእንክብካቤ አማራጮች፣ የታካሚና የቤተሰብ ድጋፍ እንዲሁም የፓሊያቲቭ ኬር መርሆዎች በስፋት ተዳስሰዋል።
“ህመምን ማከም ብቻ ሳይሆን፤ ስቃይን ማስታገስ፣ ሰውን መንከባከብ እና የኑሮ ጥራትን ማሻሻል—የተሟላ የጤና አገልግሎት መሠረት ነው።”