13/07/2026
ባህር ዳር ቅርንጫፍ ዓመታዊ የሕክምና ግብዓቶች ቆጠራን አጠናቆ ወደ መደበኛ ሥራ ለመመለስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትየኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባህር ዳር ቅርንጫፍ የ2018 ዓ.ም. ዓመታዊ የሕክምና ግብዓቶች ቆጠራን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ወደ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴው ለመመለስ ዝግጅቱን አጠናቋል።
የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሳሉ ጫኔ እንደገለጹት፣ የመጋዘን፣ የፋይናንስና ሌሎች አግባብነት ያላቸው የሥራ ክፍሎች በቅንጅትና በከፍተኛ ኃላፊነት በመሳተፋቸው የቆጠራው ሂደት ያለምንም መስተጓጎል ተጠናቋል ብለዋል።
አቶ አምሳሉ አክለውም፣ ከቆጠራው በፊት በቂ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉና ሁሉም ተንጠልጣይ ሰነዶች (Outstanding Documents) በወቅቱ በመጠናቀቃቸው የቆጠራው ሥራ በታቀደው ጊዜና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ችሏል ሲሉ ገልፀዋል።
በተጨማሪም፣ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በቅርንጫፉ የተከማቹ የሕክምና ግብዓቶች ላይ ምንም ዓይነት ብልጫም ሆነ ጉድለት አለመመዝገቡን ጠቅሰው፣ ይህንን ውጤት ለማስቀጠል በመጋዘን አያያዝ፣ በውስጣዊ ቁጥጥርና በንብረት ጥበቃ ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ፣ ለቆጠራው ስኬታማ መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉም የቅርንጫፉ ሠራተኞች ምስጋናቸውን ገልጸው፣ ተቋሙ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።