18/10/2026
ሀረሪ ክልልን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
******************
ሀረሪ ክልልን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግና የጤና አገልግሎትን ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብዲ አሚን ገለፁ።
በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየተካሄደ በሚገኘው ስራ አክሞ የማዳን አቀምን የማጠናከርና ዲጂታል የጤና መረጃ አያያዝ ስርአትን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አብዲ አስታውቀዋል።
እንደ ማሳያም በክልሉ በበጀት አመቱ ሩብ ዓመት ምንም የእናቶች ህልፈት ያልተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም በእናቶች ጤና እና የስነተዋልዶ ጤና ስራዎች የቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ ክትትል የማጠናከርና የቤተሰብ ዕቅድ ግንዛቤን የሚያሰርፅ ስራዎች ለውጤቱ ዋና አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልፀዋል።
እንዲሁም ሞተው የሚወለዱ ህፃናት ምጣኔን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ያስቻለ ስራ መካሄዱን እና በጨቅላ ህፃናት ህክምና እና እንክብካቤ በጤና ተቋም የሚድኑ ህፃናት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያስቻለ ስራ በስፋት ተካሂደዋል ብለዋል።
ይህም የክትባት አገልግሎትን ጨምሮ አስፈላጊ የጤና ክትትልና ህክምና ማቅረብ መቻሉ ያመጣው ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
በሩብ አመቱ የተሳካ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምናን ጨምሮ ከ1700 በላይ ከፍተኛ ቀዶ ህክምና በስኬት መካሄዱን ጠቅሰዋል።
በጤና በጎ ፍቃድ ስራዎች ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነፃ የህክምና እና ምርመራ አገልግሎት የተሰጠበት ስራ አካሂደናል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነፃ የአይን ሞራ ግርዶች ህክምና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
ባጠቃላይም ከ80 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ነፃ የህክምና እና የምርመራ የጤና አገልግሎት በክረምቱ የጤና በጎ ፍቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የዲጂታል ጤና ስርአትን እውን ለማድረግ ከጤና መሰረተ ልማት መስፋፋትና መዘመን አንፃር በርካታ ስራዎች በትኩረት እየተካሄዱ ይገኛልም ብለዋል።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ዲጂታል የጤና መረጃ ማዕከልና መጠባበቂያ በሀረሪ ክልል ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ በከተማና በገጠር የሚገኙ የተለያዩ ጤና ተቋማት ከወረቀት ነፃ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ስርአትን ለማጠናከር እየተሰራም ነው ብለዋል።
ከማህበረሰብ ጤና አኳያም የብዙሐን ጤና ላይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ የጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መረጃ የመሰብሰብ የማደራጀት የመተንተንና አስፈላጊ የቅድመ ጥንቃቄና የመከላከል ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ወቅታዊ የአየር ንብረት መሰረት በማድረግና የሁኔታ ግምገማ በማካሄድ ከ20 ሺህ በላይ በሚሆኑ ቤቶች የፀረ ወባ ርጭት መካሄዱን ተናግረዋል።
የጤና መድህን አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም የተናገሩት ዶክተር አብዲ ከ152 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን መረጃ ወደ ዲጂታል ስርአት የማስገባት ስራ ተካሂዷል ብለዋል።
የጤና ባለሞያዎች ቁጥጥር የማጠናከርና የመድሐኒት አቅርቦትና አግልግሎት ቁጥጥር ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጤና ተቋማትን የማዘመን፣ ንፁህና ምቹ ለማድረግ የሚካሄዱ ስራዎች መጠናከራቸውን ዶክተር አብዲ አስታውቀዋል።
በጤና ዘርፍ አጠቃላይ ስራዎች ውጤትም ሀረሪ ክልልን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለዜጎች ለማቅረብ መጠነ ሰፊ ስራዎች በትኩረትና በቅንጅት እየተካሄዱ ይገኛሉ ብለዋል።
ጥራትን ማዕከል ባደረገ አገልግሎት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ከማፍራት አንፃር ወሳኝ አበርክቶች ያላቸው ስራዎችን ስኬታማና ዘላቂ ለማድረግ የሚካሄዱ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
08/02/19